ኢሳት እና ግንቦት 7 – በእታሇማሁ ማንዯፍሮ

በአጭር ጊዜ ተጠንስሰው፣ በአጭር ጊዜ ተወልደው፣ በአጭር ጊዜ ያደጉ ድርጅቶች እንደ ኢሳትና እንደ ግንቦት7 አላየሁም ፣ ከቅንጅት በስተቀር። ኢሳትና ግንቦት 7 ስማቸው በፌስቡክ፣ በኢቲቪ፣ በዌብሳይትና በየሰዎች ቤት ይነሳል። የድርጅቶቹ ጠላቶችም ወዳጆችም ስለሁለቱ ድርጅቶች ሳይናገሩ መሽቶ አይነጋላቸውም። እውን ድርጅቶቹ እንደስማቸው የገዘፉ ናቸው? የውስጣቸውን ጥንካሬ ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት። እኔ ግን የታዘብኩትን ልናገር፣ ድርጅቶቹ በእያንዳንዲ ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ ገብተዋል። በውጭ አይደለም ፣ በኢትዮጵያ።

ባለፈው ታህሳስ አዲስ አበባ ነበርኩ። ከአዲስ አበባም አልፎ ወደ ሶስት ክልልች ተጉዣለሁ። አንዳንዶችን እንዴት ነው ነገሩ እያልኩ እጠይቃቸው ነበር። ሰዎች በመጀመሪያ የሚናገሩት ስለኢሳት ነው። “ኢሳት አይናችን ገለጠልን” ይላሉ። ታማኝ፣ አበበ፣ ሲሳይ ፣ አፈወርቅ፣ ፋሲል፣ ደረጀ፣ ገሊላ፣ መሳይ በየሰዎች አፍ ውስጥ አሉ። “ታማኝን ሰማኸው? አበበን አየኸው ” ወዘተ። ገጠር ግቡ ከተማ ፣ ወሬው ኢሳት ነው። ኢሳት ኢሳት ኢሳት.. አንድ የለውጥ ወላፈን ሲነፍስ ይሰማኝ ነበር። እነዚህ ሰዎች ባለሰብኩት ጊዜ ነገሩን ለኩሰው ፕሮጀክቴን አደጋ ውስጥ ይጥለብኝ ይሆን እያልኩ ስጋት ገብቶኝም ነበር። አልሸሽጋችሁም፣ ቶል መመለስ ፈልጌ ነበር። “ፈሪ ነሽ” ልትሉኝ ትችላላችሁ፣ ልክናችሁ ፈሪ ነኝ፣ ፖለቲካ ብወድም፣ የፖለቲካ ትግልን እፈራለሁ። በግብጽ፣ በሊቢያ ፣ በቱኒዚያ አይቸዋለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አድርጌአለሁ። ገና ያልበላሁበት ፤ ለስንቱ የህወሀት ባለስልጣን ደጅ የጠናሁበት ፤ ሴትነቴን ሳይቀር የተጠየቀኩበት ፕሮጀክት ነው። ከግልገል ባለስልጣን እስከ መምሪያ ሀላፊ ” አስቢልን እንጅ” ከማለት አልፈው ” ዳሌሽ” ያምራል እያለ በዳሌዬ ሊደራደሩ የሞከሩበትን ፕሮጀክት በአንድ ሌሊት ባጣው ዋስትናየ ምንድነው? እኔና መሰሎቼ ብንፈራ ለምን ይፈረድብናል? ወደ ተነሳሁበት ልመለስ።

የገረመኝ ህዝቡ ኢሳት ኢሳት ቢልም የኢሳትን ጋዜጠኞች ከጋዜጠኛነት ባለፈ አለመመልከቱ ነው። ታማኝ በየነ መሪያችን ቢሆን ብለው የሚናገሩ ሰዎች አጋጥመውኛል፣ አፈወርቅ ወይም ሲሳይ መሪያችን ቢሆኑ ብለው ሲናገሩ አልሰማሁም፤ ከእነርሱ ይልቅ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ነው። “ብርሀኑ መጥቶ ነጻ ባወጣን” የማይል የለም። ለውጥ አምጥቶ ተተኪው መንግስት ይሆናል ተብሎ ከ90 በመቶ በላይ የሚታመነው ግንቦት7 ወይም ዶ/ር ብርሀኑ ነው። ግንቦት7 ሲነሳ በሰዎች ዘንድ የማየው የለውጥ ተስፋ ይገርመኝ ነበር።

ህዝቡ በአገር ቤት መሪ የፖለቲካ ድርጅት አለ ብሎ አያምንም። ስለ አቶ ሀይሉ ሻውል መኢአድማ ለመስማትም አይፈልግም። ዘመናዊ የስፖርት ቤት ከፍተው፣ ባለስልጣናቱ እንዲዝናኑበት እያደረጉ ነው። “እነ እስክንድር ነጋና ብርሀኑ ነጋ ጥሪታቸውን አስወርሰው እርሳቸው ለ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ጤና መጠበቂያ ” የስፖርት ቤት ሰሩ እያሉ ሰዎች ያብጠለጥለዋቸዋል። በርግጥም የመንግስት ባለስልጣናት ስፖርት የሚሰሩበትና የሚታጠቡበት ልዩ ክፍል ሰርተውላቸዋል። ልብ በለ እኔ አይደለሁም የሰራሁት፣ ነጻ አውጭው አቶ ሀይሉ ናቸው! አቶ ሀይሉ ከመለስ ጋር የተጨባበጡት ወደው አልነበረም ለካ! እኔና እሳቸው አንድ ሆነናል፣ ቅድሚያ ለገንዘብ! አሁንም ድንበር ዘለልኩ ተመለሽ በሉኝ!

የወያኔን ጎራዴ የሚያስጥለው ግንቦት 7 ነው ብል ህዝቡ በጽኑ ያምናል። በጣም የገረመኝ ከአንድ የአንድነት ፓርቲ የከተማ ተወካይ ሰው ጋር ስንነጋገር የነገረኝ ነው ” ይህ ህዝብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቢኖርም፣ አስተሳሰቡ የቴዎድሮስ ነው፣ ስላጣን በነፍጥ እንጅ በወረቀት ይገኛል ብል አያስብም፤ ምንም ብትነግሪው ከእኛ ስብከት ይልቅ፣ የግንቦት 7ትን ሽለላ መስማት ይናፍቃል። አንድ የእኛ መሪ በኢሳት ሲቀርብ ጥቂት የሚሰማው ሰው ካገኘ እድለኛ ነው፣ አንድ የግንቦት7 መሪ ወይም ታማኝ በየነ በኢሳት ከቀረቡ ግን ከተማው ጭር ይላል። ኢሀአዴጎች እንኳ ከመንገድ ላይ የት ጠፉ ትያለሽ።”

ግንቦት 7ቶች ይህን ሲያነቡ ምን እንደሚሰማቸው አላውቅም ነገር ግን እላለሁ ህዝቡ ለእነሱ ያለው ግምት፣ እነሱ ከሚያስቡት በላይ እጅግ ግዙፍ ነው። ይህንን የህዝብ ፍላጎት ቶል ለማርካት በምን ፍጥነት፣ በምን ታዕምር መስራት እንዳለባቸው አላውቅም። እግዚአብሄር በ ቻርለስ ዲክንስ The Great Expectation ከተጻፈው ታሪክ እንዲሰውራቸው ፣ ያንን ሌት ተቀን የሚጠብቃቸውን ህዝብ ከመከራ ይታደጉት ዘንድ ከመጸለይ በስተቀር ብዙም የማደርገው ነገር የለኝም። ምናልባት ፕሮጀክቴ ትርፋማ ከሆነ ትንሽ ልቦጭቅ እችል ይሆናል፣ እሱም ገና የሚታይ ነው።

etalemahu24@gmail.com.