የብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የስልጣን መልቀቂያ ተቀባይነት አገኘ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 8/2010) የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜይቴክ/ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሕዝብና የሃገር ሃብት አባክነው ሳይጠየቁ የስልጣን መልቀቂያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ተነገረ።

ሜይቴክ የተለያዩ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችን በጊዜ ባለመፈጸምና ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት በመፈጸም ኢትዮጵያ በቢሊዬኖች የሚቆጠር ብር እንድታጣ ማድረጉን የመንግስት ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ብርጋዴር ጄኔራሉ ከሜቴክ የስራ ሃላፊነታቸው ቢለቁም በመከላከያ የስልጣን ድርሻቸው በሌላ ስራ እንደሚቀጥሉ ምንጮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ጀምሮ ያልጨረሳቸውን ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች እንዲያጠናቅቅ ጊዜ ቢሰጠውም እስካሁን ተግባራዊ አላደረገም።

እንዲያውም ለበለጠ ኪሳራ የሚዳርግ መጓተት ታይቷል ሲሉ ጉዳዩን በበላይነት የሚቆጣጠረው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በቅርቡ ለፓርላማ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ለሜቴክ ተሰጥተው ከነበሩ የስኳር ፕሮጀክቶች የጣና በለስ ቁጥር 2 የስኳር ፋብሪካ ተነጥቆ  ሌላ ኮንትራክተር ለማሰራት ምክክር እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የኦሞ ኩራዝ አንድ የስኳር ፕሮጀክትና የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎችን ሜቴክ ካሉበት ደረጃ ላለፉት 3 አመታት ፈቀቅ እንዳላደረጋቸውም ገልጸዋል።

እናም መንግስት ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል ባይ ናቸው ሚኒስትሩ።

በሌላ በኩልም ሜቴክ የአባይ ግድብ ውሃ የሚተኛበትን ሰፊ ቦታ ከደን ነጻ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን የወሰደው 2 ቢሊየን ብር እንደጠፋበትም የ”ዋዜማ” ዘገባ ያመለክታል።

በዚህ አጣብቂኝ ውስጥም ሆነ በበርካታ ቢሊየን ብሮች ብክነት የሚጠቀሰው ሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የስራ መልቀቂያቸውም በመንግስት ተቀባይነት አግኝቷል ነው የተባለው።

ይህም ሆኖ ግን በእርሳቸው ምክንያት ለጠፋው የሕዝብና የሐገር ሐብት ተጠያቂ ሳይሆኑ በመከላከያ ውስጥ ስራቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተነግሯል።

ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በሜቴክ ምክንያት ለጠፋው ችግር ሁሉ ተጠያቂ የምሆነው እኔ ነኝ ሲሉ ከዚህ ቀደም ለፓርላማ መናገራቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ሜቴክ ለሐገር መስዋዕትነት የከፈለ ድርጅት እንጂ ተጠያቂነት ያለበት አይደለም ማለታቸው አይዘነጋም።

የሕወሃቱ ጄኔራል ከአንድ ጊዜ በስተቀር ወደ ፓርላማ ብቅ ብለው አያውቁም።–ተወካያቸውን ከመላክ በስተቀር።

 

 

 

 

 

 

 

The post የብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የስልጣን መልቀቂያ ተቀባይነት አገኘ appeared first on ESAT Amharic.


Source: esat