የጠ/ሚ አቢይ አህመድ እና የፕሬዝዳንት ትራምፕ የሶሻል ሚዲያ ባላንጣነት (ሐይሉ አባይ ተገኝ)

ጠ/ሚ አቢይ እንዲህ ይሉናል:-

“ትልቁ ችግር የዲያስፓራ የኢንፎርሜሽን ምንጭ ፌስቡክ ነው። ሶሻል ሚዲያ ነው። ከዛ ይሰማና ያለቅን መስሎት የተባላን መስሎት አዛ ስቃይ ውስጥ ባገኘው አጋጣሚ ሰላም ማውረድ ሣይሆን ነዳጅ መጨመር ይሆናል ስራው። ያ! እንዲቀር እኔ የምመኘው ወልቃይት አካባቢ፤ አርማጮህ አካባቢ ያሉ በዚህም በዚያ ያሉ ዲያስፓራዎች ወደ ሃገራቸው እንዲመጡ ነው። መተው እንዲያዩት ህዝቡን። የህዝቡን ኑሮ እንዲያዩት። ህዝቡ እያለ ያለው ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያ መንገድ፣ መብራት ከዚህ ውጭ ያለው አጀንዳ የህዝብ አጀንዳ እንዳልሆነ ሲያውቁ ብዙዎቹ ሳያውቁ የሚደናገሩት ከህዝብ ጋር ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።

መፍትሄው ምንድነው መታችሁ እዩ ነው።…”

እኚህ ናቸው ‘ቀልባችንን ገዙ’ ተብሎ የተነገረን ጠ/ሚኒስትር? በርሳቸው ግንዛቤ:-

  1. ዲያስፓራውና የፓለቲካ ተቃዋሚዎች ህሊና ስለሌላቸው የሚያስብላቸው ሶሻል ሚዲያ ወይም ፌስቡክ ነው። ልክ እርሳቸው በህወሃት የራስ ቅል እንደሚያስቡት። በርሳቸው ግምገማ ዲያስፓራው ያነገበው የህዝብ ጥያቄ ሣይሆን ነዳጅ ነው። ዲያስፓራው እሣት፤ እርሣቸው “የህዳሴውን” ውሐ ይዘዋል።
  1. ዲያስፓራውን “ሲመክሩ” ነፃነትና ዲሞክራሲ እስረኛ በሆኑበት፤ የህዝብ መብት በአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ በታፈነበት ሃገር በመምጣት የህዝቡ ጥያቄ መብራት፣ ት/ቤትና ጤና ጣቢያ እንጂ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዳልሆነ እንዲረዱ ይጋብዛሉ። የተራበ ጅብ እንኩዋን በዚህ መንገድ አህያን አይጋብዝም።
  1. በእብሪትና በማንአለብኝነት በወረራ የተያዙ አርማጭሆና ወልቃይት የፍትህና የህግ የበላይነት ጥያቄ እንደሌለ ህዝብን አፈናቅለው የሠፈሩ የህወሃት ወራሪዎችን መጥታችሁ ጠይቁዋቸው ይሉናል። የአርማጮህና የወልቃይት ህዝብ የትግራይን እስር ቤት የሞሉት መብራት እንዲያገኙ ታስቦ ነው።
  1. የጆርጅ ኦርዌል ምፀታዊ መፅሃፍ ‘የእንሠሦች አመፅ (Animal Farm) ቤንጃሚን የተሠኘችው አህያ “ዝንብን እንድንከላከል ፈጣሪ ጭራ ቀጠለልን። ነገር ግን በቅርቡ ጭራ ስለማይኖረን ዝንቦችም አይኖሩም” ብላን ነበር። ጠ/ሚ አቢይም ልክ እንደ አህያዋ ቤንጃሚን ” ዲያስፓራው አርማጮህና ወልቃይት መጥቶ ቢያይ የነፃነት፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት ጥያቄ እንዳልሆነና የመብራትና የት/ቤት ግንባታ መሆኑን ከህዝቡ ይረዳል” ይሉናል። ጠ/ሚ አቢይ ልክ እንደ አህያዋ ‘ዲያስፓራው በቅርቡ የሶሻል ሚዲያውን “ቅጥፈት” ሲረዳ የነፃነትና መብት ጥያቄ አይኖረውም ሊሉን አፋፍ ደርሰዋል። በእርሳቸው “አቢዮታዊ ዲሞክራሲ” መድብል ህዝቡ ህወሃትና ሹምባሾቹን የሚቃወመው (‘ደብተርና እርሳስ ይገዛልኝ’ ብሎ እንደሚያለቅስ ተማሪ) ለመብራትና ለጤና ጣቢያ እንጁ ለፍትህና ለዲሞክራሲ አይደለም። ለዶ/ር አቢይ ወልቃይትም፣ አርማጮህም፣ ጎንደርም፣ አምቦም ወ.ዘ.ተ ተቃውሞው ከውሃ ሃይል የሚመነጭ ኤሌክትሪክ በኒውክለር ይተካ የሚል ነው።

አቢይ ያነገቡት አዲስ ሃሣብ ሣይሆን አዲስ ህዋህታዊ መልዕክት ብቻ ነው። ጠ/ሚ አቢይ ይዘው የቀረቡት የህወሃት ዕድሜ ማራዘሚያ ኪኒን እንጂ ፓለቲካዊ መፍትሄ አይደለም። ያነገቡት የነፃነትና ዴሞክራሲ ፅንስ ሣይሆን የነፃነትና ዴሞክራሲ ወሊድ ማጨናገፊያ ወይም መከላከያ ነው።

# እንደ ሔዋን በእባብ አንሣሳት።


Source: abbaymedia